1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ሮሮ ስለ ፕሪቶርያው ውል አተገባበር

ረቡዕ፣ ጥቅምት 14 2016

በፕሪቶርያው ውል መሰረት የኤርትራ ጦር እና የአማራ ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ የማስወጣት ኃላፊነቱን የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት አልፈፀመም ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ወቀሰ። የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ዓመት ሊሞላው የተወሰኑ ቀናት ይቀሩታል ።

https://p.dw.com/p/4Y1ep
Äthiopien Friedensabkommen Tigray
ምስል PHILL MAGAKOE/AFP/Getty Images

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ዓመት ሊሞላው የተወሰኑ ቀናት

በፕሪቶርያው ውል መሰረት የኤርትራ ጦር እና የአማራ ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ የማስወጣት ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት አልፈፀመም ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ወቀሰ። የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ዓመት ሊሞላው የተወሰኑ ቀናት ቢቀሩትም በጦርነቱ የተፈናቀሉ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደቀዬአቸው የሚመለሱበት ሁኔታ አለመመቻቸቱም ተገልጿል።

የሁለት ዓመቱ ጦርነት ያስቆመውየፕሪቶርያው ውል በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ከተፈረመ ዓመት ሊሞላው የተወሰኑ ቀናት ቢቀሩትም፥ የእስካሁን አፈፃፀም አጠያያቂ አልያም አመርቂ እንዳልሆነ በብዙሐን ይገለፃል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትላንት በመቐለ ከኢንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዎልች እና የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር መስርያቤት የአፍሪካ ዳይሬክተር ጀነራል ብራይት ፒክል ጋር ባደረጉት ውይይት፥ የፌደራል መንግስቱ የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ከሆኑ የትግራይ አካባቢ እንዲሁም የአማራ ታጣቂዎች ደግሞ ከተለያዩ የትግራይ የአስተዳደር ወሰኖች እስካሁን አለማስወጣቱ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ስለመሆኑ ማስረዳታቸው የፕሬዝዳንቱ ፅሕፈት ቤት ባሰራጨው መረጃ አመላክቷል።

ለዶቼቬለ የተናገሩት የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በበኩላቸውየፕሪቶርያው ውልከተፈረመ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቢቀርም በውሉ መሰረት የውጭ ሐይሎች የማስወጣቱ ግዴታ የፌደራል መንግስቱ አለመፈፀሙ ገልፀዋል። አቶ ረዳኢ "በሕገመንግስቱ ይሁን በሰላም ስምምነቱ መሰረት የኤርትራ ጦር እና የአማራ ታጣቂዎች ማስወጣት ያለበት የፌደራሉ መንግስት ነው። የፌደራሉ መንግስት ሐላፊነቱ መወጣት መቻል አለበት" የሚሉ ሲሆን የትግራይ ምዕራባዊ ዞን፣ የሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ፣ ምስራቅ እና ማእከላዊ ዞኖች የተለያዩ ክፍሎች በአማራ እና የኤርትራ ጦር ተይዘው እንዳሉ አስረድተዋል። እነዚህ ሐይሎች በትግራይ እንዲቆዩ መፍቀድ፥ የትግራይ ህዝብ "የማያባራ ችግር እንዲደርሰው መፍቀድ" ነው ሲሉም አክለዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት
የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመበት ወቅትምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ ባለው ግዜ፥ መቀመጫቸው በኢትዮጵያ ያደረጉ በርካታ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የመንግስታት ልኡካን፣ የአለምአቀፉ ተቋማት ተወካዮ፣ የኢትዮጵያፌደራል መንግስት ሚኒስቴሮች፣ የተለያዩ ክልሎች መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በትግራይ ግብኙት እያደረጉ፣ የተፈናቀሉት እየተመለከቱ፣ ከግዚያዊ አስተዳደሩ መሪዎች ጋር ሲወያዩ የሚስተዋል ቢሆንም እነዚህ ተደጋጋሚ ጉብኝቶች እና ውይይቶች እስካሁን ተጨባጭ ለውጥ አልፈጠሩም የሚሉ ትችት በርካቶች ይነሳል። በዚህ ጉዳይ የጠየቅናቸው አቶ ረዳኢ ሓለፎም ለሚመጡት የሀገር ውስጥ ይሁን የውጭ ሀገራት ልኡካን በትግራይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እያስረዳን ነው የሚሉ ሲሆን ዓለምአቀፍ ተቋማት ይሁኑ ሌሎች በትግራይ ያለው የተወሳሰበ ችግር እንዲቃለል  ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ