1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
የፕሬስ ነጻነትኢትዮጵያ

የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ደረጃ ማሽቆልቆል

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ባለፈው ዓመት ከነበረችበት በአስራ አንድ ደረጃዎች ወደ ኋላ ማሽቆልቆሏን በመረጃ ነጻነት መብት ላይ የሚሠራው “ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ” የተባለ ተቋም አስታውቋል። ኢትዮጵያ በድርጅቱ ምዘና ባለፈው ዓመት ከ180 ሀገሮች 130ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ወደ 141ኛ ወርዳለች።

https://p.dw.com/p/4fd9u
ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ
ባለፈው ዓመት በፕሬስ ነጻነት ኢትዮጵያ ከ180 ሀገሮች 130ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ወደ 141ኛ ዝቅ ማለቷን ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ የተባለው ተቋም አስታውቋል። ምስል PHILIPPE LOPEZ/AFP/Getty Images

የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ደረጃ ማሽቆልቆል

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን እና የጋዜጠኝነት ሥራ ነፃነት ባለፈው ዓመት ከነበረበት ደረጃ ማሽቆልቆሉን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ይፋ ባደረገው የምዘና ውጤት አመለከተ።

ድርጅቱ ባወጣው የ 2024 ዓ . ም የሚዲያ ነፃነት ደረጃ ኢትዮጵያ ከ180 ሀገራት 141ኛ ደረጃን መያዟን እና ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 130ኛ በ11 ደረጃዎች ዝቅ ብላ መገኘቷን አስታውቋል።  

የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት (Reporters Without Borders) ዘገባ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን ታይቶ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን ሥራ የነፃነት ዐውድ "በማንነት እና የእርስ በርስ ግጭቶች ሳቢያ ተቀልብሶ አሳሳቢ ሁኔታ መፈጠሩን" ያትታል።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 15 ጋዜጠኞች በእሥር ላይ መሆናቸውንም ገልጿል።

ኢትዮጵያ በሚዲያ ነፃነት ደረጃዋ ለምን ዝቅ አለ ?

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ችርጅት (RSF) በዓመታዊ ዘገባው ኢትዮጵያ ከደረጃዋ ያሽቆለቆለችበትን ምክንያት ሲጠቅስ በሀገሪቱ የታዩትን የእርስ በርስ እና ማንነት ተኮር ግጭቶች በቀዳሚነት አስቀምጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር እንዲወያይ ጠይቆ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።ምስል Office of Prime minister of Ethiopia

ተስፋ ታይቶበት የነበረው ያለው የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ነፃነት ወደ ከፋ ሁኔታ መዞሩን የገለፀው ይሄው ድርጅት፤ ጋዜጠኞች የመንግሥትን እርምጃ በመፍራት ሥራቸውን እንደሚከውኑ ገልጿል።

ሕወሓት እና የፌደራል መንግሥት ገብተውበት ስለነበረው ጦርነት የሚሰራጨውን ዘገባ ለመቆጣጠር ፕሮፓጋንዳን እንደ መሣሪያ መጠቀማቸውን ያመለከተው ድርጅቱ በመደበኛም ይሁን በማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮች የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨታቸውንም አመልክቷል።

የመገናኛ ዘዴዎች ሚና በብሔራዊ ምክክር

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአማራ ክልል የቀጠለው በትጥቅ የታገዘ ግጭት የጋዜጠኞችን ሥራ ጫና ውስጥ እያስገባው መሆኑን ዘርዝሯል።

ምንም እንኳን ጠንካራ የሚባል የጋዜጠኞች የሙያ ማሕበር አለ ማለት ባይቻልም ያሉትም ሀሳባቸውን እንዲያጋሩ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ጋዜጠኛ ግን ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ ተጨባጭ መሆኑን እና በዚህ ወቅት  የጋዜጠኝነት ሥራ ፈተና ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዘርፉ አሳሳቢነትና የሀገራት አስተያየት

ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገሮችን ጨምሮ  በአዲስ አበባ የሚገኙ 18 ኤምባሲዎች የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን አስመልክቶ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የንግግርና የመገነኛ ብዙኃን ዘርፍ ነፃነት "መሠረታዊ የሰዎች መብት በመሆኑ ሊከበር እንደሚገባ" ጠቅሰው ነበር።
 
ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ዛቻ እንደሚደርስባቸውና ያለ በቂ ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉም አስታውቀዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ማይክሮፎኖች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከስድስት ዓመታት በፊት ሥልጣን ሲይዙ የፕሬስ ነጻነት ይሻሻላል የሚል ተስፋ ነበርምስል Solomon Muchie/DW

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ከጋዜጠኞች ጋር እንዲወያዩ ጥያቄ ቀረበ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዚህ በሰጠው ቀጥተኛ ምላሽ ግን "በተደጋጋሚ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በመሰባሰብ በደቦ የሚወጡ መግለጫዎች ለሁለትዮሽ ግንኙነት የማይጠቅሙ ናቸው ሲል አጣጥሎታል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር እንዲወያይ ጠይቆ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ምክር ቤቱ በቅርቡ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አማረ አረጋዊ ዘርፉ የመቀጨጭ አደጋ ውስጥ መሆኑን አመልክተው ነበር።

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ከአራት ዓመት በፊት ባወጣው የሀገራት የሚዲያ ነፃነት ደረጃ ኢትዮጵያ መሻሻል አሳይታ 99 ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን 141ኛ ላይ ትገኛለች ብሏል። 

ሰለሞን ሙጬ 

እሸቴ በቀለ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር