1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ጠቅላይ ሚንስትሩ የወለጋ ጉብኝት አስተያየት

ሐሙስ፣ ግንቦት 1 2016

በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ላለፉት አምስት ዓመታ በግጭት ሲናጥ ወደ ቆየው የምዕራብ ኦሮሚያ አካል ወለጋ ነቀምቴ ስታዲየም ተገኝተው ንግግር አሰምተው ነበር ። ወለጋን የልማት እና የብልጽግና ተምሳሌት እና ማዕከል ስለማድረግም ተናግረዋል ። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ፖለቲከኛ ግን ይጠራጠራሉ ።

https://p.dw.com/p/4fg0V
Äthiopien I West Wollega - Gimbi Stadt
ምስል Negassa Dessalegn/DW

የወለጋ አሁናዊ ይዞታ፡ የነዋሪዎች አስተያየት

በትናንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ላለፉት አምስት ዓመታ በግጭት ሲናጥ ወደ ቆየው የምዕራብ ኦሮሚያ አካል ወለጋ ነቀምቴ ስታዲየም ተገኝተው ንግግር አሰምተው ነበር ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተካተቱበት የትናንትቱ የነቀምቴ ከተማ ጉብኝቱ ላይ ከአራቱ ወለጋ ዞኖች የተውጣጡ የማኅበረሰብ አካላት ታድመዋል ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወለጋን የልማት እና የብልጽግና ተምሳሌት እና ማዕከል ስለማድረግም ተናግረዋል ። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ፖለቲከኛ ግን አሁንም ያለ መሰረታዊ ውይይት እና ሁሉን አካታች ሒደት በዚያም ሆነ በመላው አገሪቱ ለልማት መነሻ የሚሆነው ዘላቂ ሰላም ስለመረጋገጥ ስለ መቻሉ ይጠራጠራሉ ።

የወለጋ አሁናዊ ይዞታ፡ የነዋሪዎች አስተያየት

ከሰሞኑ ከምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች በነዚህ ላለፉት አምስት ዓመታት በግጭት አለመረጋጋት ሲፈተን በነበረው አከባቢቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መጠነኛ መረጋጋት ቢስተዋልም አሁንም ግን ወለጋ ሰው እንዳሸው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበት አልሆነም ይላሉ፡፡ የኪረሙ ወረዳው አስተያየት ሰጪ ከወረዳቸው ወጥተው ወደ ሌላው ወረዳ ለመጓዝም አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ገና አልሰፈነም በማለት ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

"ቤተሰብ እዚሁ አጎራባች ወረዳ ጉቲን ብሞት እንኳ ከዚህ ከሀሮ ኪረሙ ተነስቶ መድረስ አዳጋች ነው” የሚሉት አስተያየት ሰጪው በቅርቡ የታየው ተስፋ በጸጥታ እጦት ወደ ከተማው የተሰበሰበው ገበሬው አሁን ላይ ወደ ገጠር ለእርሻው መመለስ መጀመራቸው ነው ብለዋልም፡፡

የወለጋ አሁናዊ ይዞታ፡ የነዋሪዎች አስተያየት
የወለጋ አሁናዊ ይዞታ፡ የነዋሪዎች አስተያየትምስል Negassa Dessalegn/DW

ሌላው የምዕራብ ወለጋ አስተያየት ሰጪም የወለጋው ግጭት ያስከተለባቸውና አሁንም ስላልተወጡት ችግር ስያስረዱ፡ "ይህ አከባቢያችን እጅግ ጥሩ አከባቢ ነበር፡፡ ተፈጥሮ በጸጋ የባረከችው አከባቢ ነበር፡፡ ፈጣሪ ምንም አልነሳንም፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ የለም፡፡ የነበረው ግጭት በማህበረሰቡ እጅ የነበረውን አውድሟል፡፡ ሕዝቡ በእጅ ላይ የለው የሚገዛበት ነገር ይቸግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ አሁን ቀን የሚገፋው በርዳታ ነው፡፡ በጣም ነው የሚከፋን፡፡ አያት ቅድመአያታችን አይተው የማያውቁ ዶፍ እኮ ነው የወረደብን፡፡ ከችግር ጋር ተገናኝተን አናውቅም ነበር፡፡ ድርቅ አናውቅ ርሃብ የለም ነበር፡፡ አሁን ግን ማህበረሰባችን አይቶ በማያውቅ ችግር ይሰቃያል፡፡ ከእጁ ያለው ጠፍቶበታል፡፡ ውሎ አዳር የለው፡፡ ታውቃለህ ስታስታውሰው አገር ጥለህ ጥፋ ያስብላል በጣም ነው የሚያሳዝነው” ይላሉ፡፡

"የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትቱ ጉብኝታቸው ባደረጉት ንግግር የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በተለይም ቋንቋን በአብነት አንስተው መመለሱን አብራርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኦሮሚያ ፖለቲካዊ ጥያቄ አለኝ፤ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ታፍኗል ያሉ የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች እና በትጥም የተደገፉ አካላት በምንቀሳቀሱበት ወቅት ነው፡፡ ይህን ንግግር ማድመጣቸውን የሚያስረዱት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና ለ50 ዓመታ ተንከባለለ ያሉት የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ተመልሷል በምለው አያምኑም፡፡ "ዋናው ጉዳይ ለ50 ዓመታት የተንከባለለው የኦሮሞ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄው መንድነው የምለውን መለየት ነው፡፡ ጥያቄው የመብት እና የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እና ኦሮሞ በሃብቱ በንብረቱ የማዘዝ ጥያ ነው” ያሉት ፕሮፈሰር መረራ ጥያቄዎቹ መሰረታዊ በሆነ መንገድ አልተመለሱም ባይ ናቸው፡፡ መረራ "ህዝቡ የበለጠ ለጥቃት የተጋለጠበት ወቅት ነው” ሲሉም ሃሳባቸውን አከሉ። 

«ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር ውስጥ እስካልተገባ ድረስ ችግሮቹን በዚህ ማለፍ ይቻላል የሚል ግምት የለንም»
«ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር ውስጥ እስካልተገባ ድረስ ችግሮቹን በዚህ ማለፍ ይቻላል የሚል ግምት የለንም»ምስል Negassa Dessalegn/DW

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትቱ የወለጋ ጉብኝታቸው ህዝቡ የተጠማውን ሰላም አስፍነው ሰፊ የልማት ክፍተት ያለበትን ይህን አከባቢ በልማት መቀየር እንደሚፈልጉ ለድጋፋቸው ለወጣው ህዝቡ አስገንዝበዋል፡፡ ፕሮፈሰር መራራ ግን በሂደቱ የተስማሙ አይመስሉም፡፡ "ህዝቡ ሰላም ቢያገኝ እኛ ደስታችንን አንችለውም፡፡ እኛ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው የሚናገሩትን እንዲኖሩ ነው የምንጠይቃቸው፡፡ መንግስታቸው የመገዳደል ፖለቲካን ወደ መደራደር ፖለቲካ እስካልቀየረ ድረስ፤ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር ውስጥ እስካልተገባ ድረስ ችግሮቹን በዚህ ማለፍ ይቻላል የሚል ግምት የለንም” ሲሉም መረራ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡

አራቱ የወለጋ ዞኖች ባለፉት አምስት ዓመታት ባመሳቸው ግጭት ንጹሃን ዜጎችን ጨምሮ በርካቶች ተገድለው ብዙዎች ከሃብት ቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር