1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህዳሴና የዓሳ ምርት፤ የአዲስ አበባዉ ጎርፍ አደጋ፤ የአውሮጳ የሕግና ፍትህ ማዕከል መግለጫ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2016

በሉ ቀልዱን ተዉትና... ኤሌትሪኩን ወዲህ በሉ የግድቡ ዋንኛ ዓላማ አሳ ሳይሆን ኤሌትሪክ ማመንጨት ነዉ፤፤ እነዛ ቢሞቱ አልቃሽ፤ ቢራቡ አጉራሽ፤ ቢታመሙ ፈዋሽ፤ ቢያለቅሱ አባሽ፤ አስታዋሽ፤ የሌላቸዉ ድሆች ይህን አድካሚ እና የመከራ ዓለም ትተዉት ጠልተዉት ሂደዋል አሳዛኝ ነዉ፤፤ ዓለም ይህን እውነታ ቀስ እያለም ቢሆን እየተረዳ መሄዱ አይቀርም

https://p.dw.com/p/4fUBn
ታላቁ የህዳሴ ግድብ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የዓሳ ምርት

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሐይቅ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑ ሰሞኑን ተዘግቧል።  ግድቡ ውኃ መያዝ ከጀመረ ወዲህ በተለይም ለዓሳ ማስገር ምቹ መሆኑን በአካባቢው ዓሳ አስጋሪ ወጣቶች ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ከአንድ መቶ በላይ ወጣቶች በዚሁ ስራ መስክ እንዲሰማሩ በማህበር ማደራጀታቸዉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡ የቢሮው ኃላፊ በ8 ወራት ውስጥ 1729 ቶን የዓሳ ምርትከህዳሴ ግድብ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ በግደቡ ዳርቻ በቀን ከ 2 እስከ 3 ኮንታል ማለትም  250 ኪሎ ግራም ዓሳ እንደሚያገኙ ነዉ የተነገረዉ።   

ሰላማዊት ሰሌና ኩራ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ በሉ ቀልዱን ተዉትና... ኤሌትሪኩን ወዲህ በሉ። የግድቡ ዋንኛ ዓላማ አሳ ሳይሆን ኤሌትሪክ ማመንጨት ነዉ ብለዋል። 

ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ሌላዉ አስተያየት ሰጭ ሃፍቶም ሃይላይ ናቸዉ ። ይህን ግምት ዉስጥ በማስገባት ነበር፤ መለስ ዜናዊ ግድቡን የጀመቱት ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ዮናታን ከማል እንዲህ ይላሉ ድንቅ የሆነ ስራ፤ ለስራ መሰማራት ብቻ ሳይሆን ለንግድ ለአምራችነትም መዘጋጀት ግድ ይላል ሲሉ አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ ቋጭተዋል። ኬልቪን ስቴዋርት የሚል የፌስቡክ መለያ ያላቸዉ በአስተያየታቸዉ፤ እንኳን አሳ ፤ አሳነባሪ ቢያጠምዱ የኢትዮጵያ ኑሮ ፈቀቅ አይልም። ዘላለም ድህነት ብቻ ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። 

ተመስገን የኋላ እሸት፤ እና ይላሉ  እና እኛ ህይወት ላይ ምን ይፈጥራል?፤  አይደለም አሳ ነዳጅ ቢወጣ ለኛ ከመስማት በስተቀር ምንም አይፈይድም። ጉራ እና ወሬ ብቻ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ወንድዬ ኃይሉ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ፤ ግን እኮ ይላሉ፤ ግን እኮ የቆርቆሮ አሳ ሰርዲን ማለታቸዉ ነዉ፤ የቆርቆሮ አሳ 350 ብር እየገዛን ነው። ለዛውም ሚጢጢዋን ሲሉ በአራት ነጥብ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ዓባይ ለካስ ግንድ ሳይሆን ዓሣ (ምግብ ) ነበር ይዞ የሚዞረው? ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ያበቁት ደግሞ ታማኝ ኃይሌ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ። 

ጌታቸዉ መርጊያ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ እንዲህ ይላሉ፤ ተባብሮ መብላት ነው፤ ለሁሉም ይበቃል። መናናቅን ትተን ፊታችንን ወደልማት ብናዞረው መጥፎው ነገር ሁሉ ተረት ተረት ሆኖ ይቀራል፤ ብለዋል። መስተዋል ሳገኝ የተባሉ አስተያየት ሰጭም  ተመሳሳይ አይነት ሃሳብ  ነዉ ያስቀመጡት ፤ ይህ ጅማሮ ነዉ ይላሉ ይህ ጅማሮ ነዉ። ገና ምን ታየና። ኢትዮጵያ ወደ ታላቅናቷ ትመለሳለች።  

የአዲስ አበባዉ አሳዛኝ የጎርፍ አደጋ

አዲስ አበባ ዉስጥ ባለፈዉ እሁድ ከእኩለ ለሌት ጀምሮ  የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለዉ ጎርፉ በትንሹ የ 14 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ከጎርፍ አደጋው የተረፉ እንዳሉት ፤ ድንገተኛዉ ጎርፉ የወሰዳቸዉ ሰዎች ጎዳና ላይ ቱቦ ዉስጥ የሚያድሩ ችግረኞች ናቸዉ ። የዓይን ምስክሮቹ እንዳሉት በተኙበት ከአጠገባቸዉ በጎርፍ ከተወሰዱት ሰዎች እስካሁን የተገኘዉ የ8ቱ  አስከሬን ብቻ ነዉ። ከአዲስ አበባዉ አደገኛ ጎርፍ ቀደም ብሎ በኬንያ በተለይ መዲና ናይሮቢ የዉኃ መጥለቅለቅ እና ጎርፍ ቢያንስ  ወደ 100 ያህል ሰዎችን ገድሏል በአስር ሽዎች የሚቆጠሩትን አፈናቅሏል። በዩጋንዳም እንዲሁ ጎርፍ ጉዳት አድርሷል።

የአዲስ አበባዉን አሳዛኝ አደጋ በተመለከተ ነፍስ ይማር ሲሉ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮች ሃዘናቸዉን ገልፀዋል።  

 ኬንያን የመታዉ ከፍተና ጎርፍ፤ ናይሮቢ
ኬንያን የመታዉ ከፍተና ጎርፍ፤ ናይሮቢ ምስል IMAGO/Xinhua

ፍቃዱ ጉተማ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ እነዚህ ልጅች ከደቡብ ክልል ወደ ከተማው የገቡ ናቸው። በተደጋጋሚ ጊዜ በየዓመቱ ተደብቀው ድልድይ ስር ከፖሊስ ተደብቀው እየሾለኩ ወንዝ ውስጥ የሚያድሩ ናቸው፤ ክፍለ ከተማዉ በቆርቆሮ መግብያውን ቢያጥረውም በድልድዩ ተደብቀው፤ ቁጥቋጦ በበዛበት ጫካ ነገር ውስጥ ገብተው ይተኛሉ።  ይህ ቦታ ለመግባት አስቸጋሪ ስለሆነ፤  በጉልበት ከፍ ያሉት አስገድደው ህፃናትን ሴቶችን ከገጠር እያመጡ ይሰበስባሉ።  በየዓመቱ ወንዝ ይወስዳቸዋል። ማንነታቸዉ ስለማይታወቅም ተዳፍኖ ይቀራል፤ እንጂ በየዓመቱ ውኃ እንደወሰዳቸው ነው። ዘንድሮም እንደዛው ፖሊስ በተከታታይ ከዛ እንዲርቁ ሲያደርጋቸዉ ነበር። ነገር ግን ማታ ላይ ብዙዎች  በድልድይ ስር ሾልከው ይደበቃሉ ሰለባም ይሆናሉ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። 

ዘለቀ ቢተዉልኝ፤ እነዛ ቢሞቱ አልቃሽ፤ ቢራቡ አጉራሽ፤ ቢታመሙ ፈዋሽ፤ ቢያለቅሱ አባሽ፤ አስታዋሽ፤ የሌላቸዉ ድሆች ይህን አድካሚ እና የመከራ ዓለም ትተዉት ጠልተዉት ሂደዋል አሳዛኝ ነዉ። አንዱ ቪላ ቤቶችን ስርቶ ውበታቸዉ እያስጨነቀው ሲታመም፤ ሌላው መጠጊያ አጥቶ ቀን በፀሐይ፤ ሌት በብርድ በቁ፤ር በቆፈን፤ ሲሰቃይ በየሽንት ቤቱ ቱቦ ሲተኛ፤  ይህው፤ ለዚህም፤ ተቀንቶባቸዉ፤ ጎርፉ ቤቱ የኔ ነዉ፤ ማንፈቀደላችሁ ብሎ፤ ይዟቸዉ እብስ አስከሬናቸዉ እንኳን ፈልጎ ለማግኘት ከባድ ሆንዋል፤ ባለቤቱ ማን ይሆን ? ያሳዝናል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። መሲ ቸኮል የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ ወገኖቼ በዚህ የተፈጥሮ ክስተት የሚፈለገው ፀሎት እንጂ ቢሂሎች መሆን የለበትም። ከድንገተኛ አደጋ ፈጣሪ ይሰውረን። ለወገኖቻችን ደግሞ እግዚአብሔር ነብሳቸውን ይቀበልልን  ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

የአውሮጳ የሕግና ፍትህ ማዕከል መግለጫ

የአውሮጳ የሕግና ፍትህ ማዕከል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የአማራ ኅብረተሰብ «ብርቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት» ይፈጸምበታል በማለት ጥልቅ ምርመራ ያደረገበትን ዘገባ ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። «የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ያልተነገረለት ስቃይ» በሚል ርእስ ማዕከሉ ይፋ ባደረገዉ በዚህ ባለ 18 ገጽ ዘገባ፣   «ከጅምላ ጭፍጨፋ እስከ ድሮን ጥቃት» ደረሰ ያለውን ግድያ በዝርዝር አስቀምጧል። በዘገባዉ መሠሰረትም ማዕከሉ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) 47ኛው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ግምገማ የሚሆን ደብዳቤ ማስገባቱንም ይፋ አድርጓል ። ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ላይ የሚወያየው የተመድ 47ኛው ጉባኤ በሚቀጥለው ዓመት ከጥቅምት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ11 ቀናት የሚካሄድ ነዉ ተብሏል።

አዉሮጳ ህብረት አርማ እና የፍትህ ምልክት
አዉሮጳ ህብረት አርማ እና የፍትህ ምልክትምስል DesignIt/Zoonar/picture alliance

ርዕሱ ስር በርካታ አስተያየት ሰጭዎች የሚዲያችን መስፈርት የማይጠብቁ በርካታ አስተያየቶች የተሰጡበት በመሆኑ አንድ ሁለቱን መራርጠን ይዘናል።  ሲሳይ አበበ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ በጉዳዩ ላይ የተሳቱፉ የፖለቲካ እና የጦር አዛዦች ህግ እንዲጠየቁ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።  እጅጉ ወርቁ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ፤ ግፉ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው። ዓለም ይህን እውነታ ቀስ እያለም ቢሆን እየተረዳ መሄዱ አይቀርም ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል። ፍትህ ለደጉ ህዝብ ሲሉ አስተያየታቸዉን የፃፉት ደግሞ እዩም ሃበሻ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ።  

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ